በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት አስመልከቶ ለሴናተር ሮይ ዋይደን ገለጻ ተደረገ

የአማራ ማህበር በኦሪገን የስራ አመራርና የቦርድ አባላትን እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚወክሉ 12 አባላትን ያካተተ ልዑክ  በአማራ ህዝብና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ በብልጽግናው መንግሰት እየደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት ድርጊት ለህዝብ እንደራሴው ሮይ ዋይደን ገለጻ አደረጉ። የተሰጠው መግለጫ በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን የጅምላ ጭፍጨፋ፣ ግድያ፣ መፈናቀል፣ ከስራ መሰናበት፣ እገታ፣ ስደት፣ የጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና ፖለቲከኞች ያለ ፍርድ መታሰርን ያካተተ ነው። የመሰብሰብ፣ ሃሳብን በነጻነት የማራመድና የመያዝ መብት በአገዛዙ ስለመገደቡና ይህን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት በሀገሪቱ ህግ መሰረት ለማካሄድ በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ላይ አማራ በመሆናቸው ብቻ የዚህ መብት ተሳታፊ እንዳይሆኑ አገዛዙ የሚያደርገውን አምባገነናዊ ድርጊት በማስረጃ በማስደገፍ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

አረመኔው የብልጽግና መንግስት የአማራ ነው ያለውን ባህል፣ እምነትና ታሪክ እንዴት እያጠፋ እንደሆነ በምስል ማስረጃ ተደግፎ ቀርቧል። የባህል መገለጫዎቹ፣ ቤተ እምነቶቹና ታሪካዊ ቅርሶቹ መውደማቸውን፣ በተለይ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከ100 ዓመታት በላይ እድሜ ያላቸውን አብያተ ክርስቲያናት ከእምነቱ ተከታዮቻቸው ጋር መቃጠላቸው ተገልጿል።

ከመጋቢት 2015 ዓም በክልሉ አገዛዙ ጦርነት ካወጀ ጊዜ ጀምሮ ከአራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መከልከላቸው፣ ት/ቤቶች በድሮንና በከባድ መሳሪያ በአገዛዙ መውደማቸው፣ ከውድመት የተረፉትም በወታደር ካምፕነት እያገለገሉ ስለመሆናቸው ተብራርቶለቸዋል።

በተጨማሪም በክልሉ ያሉ የጤና ማዕከላት አገልግሎት እንደማይሰጡ፤ ህጻናት፣ እናቶችና አረጋውያን መታከም ከማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸውና በህክምና እጥረት በርካቶች ለሞት ስለመዳረጋቸው ገለጻ ተደርጓል።

ይህንን ማለቂያ የሌለው አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ድርጊት እንዲቆም የህዝብ እንደራሴዎች ጫና በማድረግ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ፣

  • በተለይም ደግሞ በአሜሪካ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውን House Resolution 937 እንዲጸድቅና እንዲተገበር ድጋፍ እንዲያደርጉ፣
  • በአማራ ህዝብና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያጣራ ዓለም ዓቀፍ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን እንዲቋቋም ግፊት እንዲያደርጉ፣
  • የአሜሪካ መንግሰትም ሆነ ሌሎች ዓለም ዓቀፍ አበዳሪ አካላት ለኢትዮጵያ መንግስት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጤኑ፣
  • በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚካሄደው ጭፍጨፋ የገንዘብና የመሣሪያ ድጋፍ የሚያደርጉ ሀገራትን UAE, Turkye, Iran የመሳሰሉ ሀገራት የሚያደርጉትን የመሣሪያና የገንዘብ ድጋፍ እንዲያቆሙ ጫና እንዲደረግ ተጠይቋል።

የሴናተር ሮይ ዋይደን ጽ/ቤት ኃላፊዎች ወይዘሮ ኤልዛቤል ቱርነር እና ወይዘሮ ግሬስ ስትራቶንበበኩ ላቸው በገለጻው በኢትዮጵያ በአማራና በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ በመንግስት እየተፈጸመ ያለውን አሰቃቂ ድርጊት ላይ በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ ገልጸው ጽ/ቤታቸው ጉዳዩን በጥልቀት መርምሮ በምን መንገድ እገዛ እንደሚያደርግ ያሳውቃል ብለዋል። የአማራ ማህበር በኦሪገን የሚያደርገውን ማህበረሰብ ተኮር እንቅስቃሴዎች አጠናክሮ እንዲቀጥልና ማህበሩ ድምጹን ማሰማት እንዲችል በኦሪገን ግዛት በሚደረጉ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እንዲወከል እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል። የማህበሩ የሥራ አስፈጻሚዎችና የሃይማኖት አባቶች በዝግጅቱ ላይ ተገኝተው ማብራሪያና ጥያቄዎችን አንስተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *