የአውሮጳ የሕግና የፍትህ ማዕከል (European Centre for law and Justice ) ባለሥልጣናት ዛሬ ከቀትር በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶችን የተመለከተ ገለጻ ተደረገ።
የአውሮጳ የሕግና የፍትህ ማዕከል (European Centre for law and Justice ) ባለሥልጣናት ዛሬ ከቀትር በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶችን የተመለከተ ገለጻ ተደረገ። የአውሮጳ የሕግና የፍትህ ማዕከል ከቀናት በፊት ሽትራስቡርግ ፈረንሳይ በሚገኘው የሕብረቱ ምክር ቤት በጎን በሚካሄድ መድረክ ኢትዮጵያውን ላይ እየተፈጸመ ስላለ ወከባና ጥቃት እንደሚያደምጥ ዐሳውቆ ነበር። በቀጠሮው መሠረትም በዛሬው ዕለት የመድረኩ ዋነኛ ተናጋሪ ልዑል ዶክተር አስፋወሰን አሥራተ፤ በተለይ «በዝምታ የሚፈጸመው የአማራ ስቃይ» በሚል ርዕስ ዝርዝር ገለጻ አድርገዋል።
ልዑል ዶክተር አስፋወን አስራተን በማስተዋወቅ የጀመሩት መድረኩን ከጋበዙት የአውሮጳ ምክር ቤት አባላት አንዱ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፦ «ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ አቅጣጫ ብቻ የእርስ በእርስ ጦርነት ብቻ ያለ ይመስለኝ ነበር» ያሉ ሲሆን፤ ከሚደርሷቸው መረጃዎች ግን ጥቃት ግጭቱ በየቦታው መሰራጨቱን መረዳታቸውን ተናግረዋል።
ዶክተር አስፋወሰን በበኩላቸው በገለጻቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በሲቪሎች ላይ እየተፈጸመ ነው ያሉትን ጥቃት እና ግድያ መንግሥት ማስቆም አልቻለም ሲሉ ወቅሰዋል። «ብዙ ጊዜ የመንግሥት ሚና ምንድነው እያልኩ እጠይቃለሁ» ያሉት ልጅ ዶክተር አስፋወሰን አስራተ፤ ቅድሚያ የሕዝቡን ደኅንነት ማስከበር የመንግሥት ኃላፊነት እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአፍሪቃ ኅብረትን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትን በምታስተናግደው ታሪካዊት ሀገር ኢትዮጵያ የግለሰቦችና የሀገር ደኅንነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን በመግለጽም፤ ይህ ሁሉ በቂ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋንና ትኩረት እንዳላገኘም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸመ ነው ላሉት ዘርና ሃይማኖትን መሰረት ላደረገ ጥቃት ተጠያቂነት እንደሌለ በማመልከትም ፍትህ እና ተጠያቂነት እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።
በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥትም ሆነ በታጣቂ ኃይሎች የሚፈጸሙ የጦር ወንጀሎች፤ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀልና የዘር ፍጅት ተጠያቂነት የሌለበት ነው ሲሉም ተችተዋል። ገለጻውን ካደመጡ የአውሮጳ ፓርላማ አባላት አንዱ፤ «ለምድነው መንግሥት የራሱ ሕዝብ ላይ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን)ም ሆነ በሌሎች የጦር መሣሪያዎች ጥቃት የሚያደርሰው?» ሲሉ ጠይቀዋል።
በምላሻቸው «ኢትዮጵያ ውስጥ የክፉ ነገሮች ሁሉ ምንጭ ሕገ መንግሥቱ ነው» ያሉት ዶክተር አስፋወሰን፤ «ከዓለም በጎሳ ላይ የተመሠረተ ፌደራሊዝም ያለባት ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ» እንደሆነችም ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም በርካታ ጎሳዎች ባሉባቸው የአፍሪቃ ሃገራት የፖለቲካ አካሄድ «አንድነት በልዩነት ፤ ልዩነት በአንድነት» የሚል መሆን እንደሚገባውም ሃሳባቸውን አጋርተዋል።
Source: https://www.facebook.com/share/p/1A7KWLq2DJ/
