ከሀገር ቤት የተላከ ደብዳቤ

ይድረስ ለልጆቼ ከአባታችሁ።

እንዴው ለመሆኑ ሰላም አላችሁ? ጤንነታችሁ እንዴት ነው? እኛ ደህና ነን። እድሜ ለእናንተ ደህና ነን። እንዴው ሁኔታው ግን ያስፈራል። ግፉ በዛ። ሞት በሁሉም ቤት እየገባ ነው። የኛ ተራም እስኪደርስ ድረስ እንቆዝማለን። ለመሆኑ አማሪካ ችግር ገጠማት እንዴ? በሰልፍ ተናወጠች ብሎ እኮ የአያ ጥላሁን ልጅ በሰፊው አጫወተኝ። ይገርምሃል ትምህርቱን ከዩኒበርስቲ ተመርቆ ከተመለሰ ጊዜ ጀምሮ ስለ ውጭው እና ስለ ሀገራችን በሞባይሉ ይነግረኛል። እንዲያ እሳት የነበረ ተማሪ ኮሌጅ በጥሶ ከእኔ ከሽማግሌው ጋር ሰፈር ለሰፈር ሲውል እንዴት አንጀት ይበላል መሰለህ። የመንግስት ሹማምንት ይመጡና ውትድርና ልውሰድህ እያሉ ስለሚያስቸግሩት እነሱ መጡ በተባለ ቁጥር ጫካ ውስጥ እየዋለ እያደረ ያመልጣቸዋል። ከሰሞኑ መጥተው ቢያጡት ያን ጠንካራ ገበሬ አባቱን ካላመጣኽው እንደፋሃለን ብለውታል። አስጨናቂ ጊዜ ነው ልጆቼ። የራሳችን ጎረቤቶች ወረዳ ሂደው እየጠቆሙ ስንቱን ወጣት ወደ ውትድርና እንዲጋዝ አደረጉት መሰለህ። የእኔ ነገር ለመሆኑ ምን ይፈጠር ብላችሁ ነው በአማሪካ ላይ ሰልፍ የወጣችሁት። ሰው በሃገሩ ስንት ግፍ እየደረሰበት ተሸክሞ ዝም ብሎ የለም እንዴ!

መቼም ያልታደለ አማራ ይውጣ አልተባለም አይደል? መቼም የእኛ ጉደኞች እንደሚያደርጉት ማኅጸን ተርትረው ጽንስ አላወጡም አይደል? በጥይት ሳይሆን በገጀራ ከትክተው አልገደሉም አይደል? አማራ እየተለየ እንደሚሳደደው የመንግስት ወታደሮችና ደጋፊዎቻቸው በዘር እየለዩ አላሰሩም አይደል? ከቤታችሁን አውጥተው ሜዳ ላይ አልጣሏችሁም አይደል? እኔማ የሀገር ቤቱ እጣ ፋንታ ተከትሏችሁ ሄደ ይሆን ብየ በጣም አዘንኩ። ደግሞ ልጁ እንደነገረኝ በብዙ ከተሞች በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ነው አሉ በአንድነት ለተቃውሞ የወጣው። ደግሞም ዳቦና የመኪና ላምባ ተወደደብን እና ጦርነት ይቁም ብላችሁ ነው እንጂ ከላይ ያነሳኋቸውን አይመለከትም አለኝ። ታድለው አልኩ። እንዲህ ተጠራርቶ በማይመች መንግስት ላይ ማመጥ።

እንዴው ለመሆኑ የምንገዛው ላምባ ከ12 ተነስቶ ዛሬ 150 ብር ሲገባ፣ ባጠቃላይ ኑሮው ሰማይ ሲነካ፣ ይኸው አብይ የሚባል ህዝቡን ገዳይ ጦረኛ መሪ ከመጣ ጊዜ ሀገራችሁ ከባሩድ ሽታ፣ ከሰው ግድያ፣ ደም ከማፍሰስ መቸ ቦዝና ታውቃለች። በተለይ የፈረደበት አማራ ተዘቅዝቆ ሲሰቀል፣ እሬሳው በአህያ ጀርባ ተጭኖ በአደባባይ ለእይታ ሲበቃ፣ ወላድ አማራ ማኅጸኗ ሲተረተር፣ እትብታቸው የተቀበረበትን ሰርተው ያቀኑትን፣ በላባቸው ያፈሩትን ንብረት ጥለው ሲሰደዱ፣ ሰዎች፣ ከብቶች በጅምላ በቤት ውስጥ ሲቃጠሉ፣ የአማራ ቤት እየተለየ ሲፈርስ፣ ከስራ ገበታው ሲፈናቀል፣ ነፍስ አውጭኝ ብሎ ሲሰደድ በባህርና በበረሃ ሲያልቅ፣ ቢያንስ ለሰማይ ቤታችን እንኳን ስንቅ እንዳይኖረን ቤተ እምነቶቻችን ሲቃጠሉ መቸ ይሆን አማሪካ ለእኛ ሰልፍ የምትወጣው?

አማሪካ አልኩ የእኔ ነገር እንዲያ ቢጨንቀኝ እኮ ነው። እንኳን በመላው አማሪካ ያለውን አማራ ልታስተባብሩ ይቅርና እናንተ እንኳን ስንት ጊዜ የምትቀያየሙት። እኔማ ዝም ብየ ሳስበው እንዴው ይህን አማራ የሚባለው ህዝብ በስደት ሆኖ እንኳን በአንድነት እንዳይቆም ምን አዚም ጣለበት ብየ ፈጣሪን እጠይቃለሁ። አንዳንዴ ሞቴን እመኝና ደግሞ መልሼ የአማራን ትንሳኤ ሳላይ አትውሰደኝ ብየ ፈጣሪን እማጸናለሁ። ባለፈው እመጣለሁ ስትለኝ ማስቀረቴ ፍጡነ ረድኤቱ ነው የረዳኝ። ከሰሞኑ የአያ ጥሩነህ ልጅ እናቱ አሟት ልጄ መጥቶ ካላየኝ ብላ ነው አሉ ከአማሪካ መምጣት። አዲስ አበባ እንደደረሰ ስልክ ሲመታ በነጻ አውጪዎቹ ፋኖዎችና በዜጎች ገዳይ ወታደሮች መካከል ጦርነቱ አይሎ መንቀሳቀስ አይቻልም ነበር። አዲስ አበባ ትንሽ እንደቆየ ነጻ አውጭዎቹ ስራቸውን ጨርሰው ወደ ቦታቸው ሲመለሱ እናቱን ለማየት ወደ ገጠር ይዘልቅልሃል። ከእናቱ ሳይደርስ መንገድ ላይ ታግቶ በብዙ ሚሊዮን ብር አምጡ የሚል ስልክ ይደወላል ለቤተሰቡ። ብሩ ከየት ይምጣ። በድርድር ግማሽ ያህሉን ብር ከሰጡ በኋላ እናቱን ሊጠይቅ የመጣ ጀግና ገድለው ከገዎቻው አለፍ ብሎ ያለውን ጎድጓዲትን ታውቀው የል? ከሱ ላይ ሬሳውን ጥለው ጠፉ። እንዴት አንጀት ይበላል መሰለህ። አቤት እናቱ ጸጸቷ። የሽንቁሪት ቀበሌ በሙሉ እንባውን አፈሰሰ። በእንባ አይመለስ ነገር።

በማግስቱ ዘመድ አዝማዱ ተሰባስቦ ብሩ የገባው በመንግስት ባንክ ቁጥር ስለሆነ የሰዎቹ ማንነት ይታወቅና ይያዙልን ብሎ ሲያመለክት ማን ስጡ አላችሁ ብሎ ብር ያሰገባውን ሰው አሰሩት። ግራ የሚያጋባ ዘመን እኮ ነው የገጠመን።

ልጆቼ መቼም ዘንድሮ እግዚአብሔር እንኳን ባይገለኝ የአብይ አሞራ መቼ እንደሚገለኝ አላውቀውም። ባለፈው ጤና ጣቢያውንና ትምህርት ቤቱን በገዳይ አሞራው ሲያወድም ገበያ ሲመለሱ የነበሩ ሰዎችን ገደለች። ደግሞ ስትተኩስ ጩኸቷ የምጽአት ቀን ነጎድጓድ ነው የሚመስለው። እንዴት ያስጨንቃል መሰለህ። ግን ሳልሞት ሀገር ሰላም ሆኖ ባያችሁ ብየ እመኛለሁ። በተለይ የአማራ ሰቆቃ ተገትቶ ማየት እንደገና መወለድ ነበር። ስንት ጀግና አናብስቶች አሉ መሰለህ። ደሞዝተኛ ገዳይ ወታደር የእነሱን ጥይት ሲሰማ መድረሻ ነው የሚጠፋው።

ለመሆኑ ልጁ እንደነገረኝ ይች አማሪካ የምትባል ጉደኛ ሀገር አምባገነን መሪዎችን አንቃ ከቤተ መንግስት ትወስዳለች አሉ። እና የእኛንም ገዳይ መሪ አንቃ እንድትወስድልን ለምን አትነግሯትም። ለምን በአንድ ላይ ሁናችሁ በሀገራችሁ እየሆነ ያለውን ሰቆቃ ለአማሪካ አትነግሯትም። ህዝቡም ሰላም አግኝቶ ሰርቶ ኑሮውን ቢያሸንፍ።

ከመጨረሴ በፊት አንድ የምስራች ልንገርህ። መላው የሽንቁሪት ቀበሌ ሰው ቤተስኪያን ተሰባስቦ ይህን ክፉ ጊዜ ተጋግዞና ተባብሮ ለማለፍ ተማምሏል። ከዚህ ቀደም ቁርሾ ያለው ሁሉ ቂሙን ትቶ በአንድነት ለመቆም ተማምሏል። ለጀግኖችም ድጋፍ ለማድረግ ተስማምቷል። እኔም እናንተ ከምትልኩልኝ ገንዘብ ቆንጠር እያደረግሁ አስተዋጽኦ አደርጋለሁ። እናንተም የእኛን ፈለግ ተከተሉ። አንድ ሁኑ። እኛ ገበሬዎች እንዳንበልጣችሁ አደራ። ተሰባስባችሁ ለአማሪካ ንገሯት ነጻ ብታወጣን።

በሉ በጸሎታችሁ አስቡኝ እኔም አስባችኋለሁ። በሌላ ጊዜ ደግሞ የሚመጣ ሰው ሳገኝ እልካለሁ። አባታችሁ ከሽንቁሪት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *