አንድነታችን ማጠናከር ወቅቱ የሚጠይቀው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው ሲሉ በኦሪገን የአማራ ተወላጆች ገለጹ። በኦሪገን የአማራ ማህበር አጠቃላይ ስብሰባ ላይ አባላቱ እንደገለጹት በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን የሰብአዊ ቀውስ በሚቻለው መጠን ለመደገፍም ሆነ ለዓለም ድምጽ ለማሰማት በጋራ መቆም ወሳኝ መሆኑ በአጽንኦት አባላቱ ገልጸዋል።
በ2025 ዓ.ም ማህበሩ በርካታ ስራዎችን መስራቱን በቀረበው ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል። ከተሰሩ ስራዎች መካከልም በአገዛዙ በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ ለኦሪገን መንግስትና ለፌዴራል መንግስቱ የህዝብ እንደራሴዎች ተገቢው መረጃ እንዲደርሳቸው ተደርጓል። ከዚህም በተጨማሪ ለተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ የሚውል የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ ተሰርቷል። የአባላት ቁርጠኝነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የማህበሩ አመራር የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ለማሰባሰብ ተሞክሯል። ይሁን እንጂ ጊዜን ሰጥቶ በቁርጠኝነት የመሰባሰብና የሚጠበቀውን ያህል አስተዋጽኦ ማድረግ አልተቻለም።
አባላቱ በበኩላቸው የመረጃ ክፍተቶች እንደነበሩ ጠቁመው ይህን ክፍተት በማረም አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ትኩረት ተሰጥቶታል።
በመንግስት እየተመራ በአማራ ላይ የሚፈጸመውን ግፍ እየተከታተሉ ለአባላቱ፣ ለተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ድርጅቶች፣ ለአሜሪካ ባለስልጣናት በማሳወቅ፣ የምናገኘውን ሚዲያ በመጠቀም ድምጻችንን በማሰማት ግፉ ፍጻሜ እንዲደርስና የአማራ ህዘብ ህልውና እንዲረጋገጥ በትጋት እንደሚሰራ አጽንኦት ተሰጥቶታል።
የአማራ ህዝብ አንደኛ አምራች ህዝብ ሆኖ ሳለ ላለፉት 50 ዓመታት በተሰራ መንግስት መር ግፍ ድጋፍ ፈላጊ መሆኑ እጅግ የሚያስቆጭ ጉዳይ በመሆኑ ድምጻችንን ከማሰማት ባለፈ ተጨባጭ ድጋፎችን በማድረግ ዘላቂ አምራች እንዲሆን መስራት ወሳኝ መሆኑ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በፋኖ ላይ የነበረው መከፋፈል በኦሪገን ኗሪዎች ላይም ተጽእኖ እንደነበረው አውስተው አሁን የተፈጠረው አንድነት ጥሩ አጋጣሚ ስለፈጠረ በአንድነት መንቀሳቀስና ተጨባጭ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል ብለዋል። ሁሉም አማራ በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለአማራ ግፍና መከራ ማሳወቅ ያስፈልጋል።
በስብሰባው ወቅት የ2026 ዓ.ም አመታዊ ዕቅድ ቀርቦ በውይይት ከዳበረ በኋላ ጸድቋል።
