ድርቅ በአማራ ክልል

በአማራ ክልል ያለው የሰብአዊ ቀውስ እየተባባሰ መሆኑ ኗሪዎቹ እየገለጹ ነው። በተለያዩ ብዙሃን መገናኛ አውታሮች በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ አማካይነት ከስፍራው የሚደርሱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአገዛዙ ከሚፈጸም የጅምላ የድሮንና የከባድ መሣሪያ ጭፍጨፋ በተጨማሪ በተለያዩ የክልሉ ወረዳዎች በከፍተኛ ድርቅ እየተመቱ ነው። እንስሳት የሚበሉት መኖ አጥተው እየሞቱ ነው፤ የተዘሩ ሰብሎችም ለፍሬ ሳይበቁ እየደረቁ ነው፤ ዝናብን ተስፋ አደርገው የታረሱ ማሳዎች ጦም አድረዋል። በርካታ ሰዎችም ቤታቸውን በመዝጋት ህይዎታቸውን ለማትረፍ ወደ ከተማ እየተሰደዱ ሲሆን የአገዛዙ አመራሮች “ገጽታን ያበላሻሉ” በማለት ወደ ዋና ዋና ከተሞች እንዳይገቡ በማድረግ በቀያቸው ሆነው ያለምንም እርዳታ እንዲሞቱ እየተፈረደባቸው መሆኑን ተዘግቧል። ድርቁ በአማራ ክልል በጎንደር ጠለምትና በዋግ ኽምራ ወረዳዎች ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን በአካባቢው ያሉ ኗሪዎች የተናገሩ ሲሆን በሀገሪቱ የተከሰተው ድርቅ አድማሱን በማስፋት በትግራይና በአፋርም እንስሳት እየሞቱና ኗሪውም ቀየውን ለቅቆ እየተሰደደ መሆኑ ተዘግቧል። አፋጣኝ ድጋፍ ማድረግ ካልተቻለ ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል ተገልጿል። የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መንግስት ለሚያጎርሰው ሳይሆን  በጅምላ ለሚተኩሰው የጦር መሣሪያ ትኩረት ማድረጉ አሳዛኝ ነው ሲሉ በርካታ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ያስረዳሉ።