በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት አስመልከቶ በአማራ ማህበር ኦሪገን የኦሪገን ሁለተኛ እንደራሴ ለሆኑት ሴናተር ጀፍ መርክሌይ ገለጻ አደረገ።

የአማራ ማህበር ኦረገን በጁን 18 ቀን 2026 ዓ.ም ከሴናተር ሮን ዋይደን ጋር ገለፃ መደረጉ ይታወቃል። በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ ለአሜሪካ የህዝብ እንደራሴዎች የማሳወቅ እንቅስቃሴውን አጠናክሮ በመቀጠል ጁን 30,2026 በኦሪገን የህዝብ እንደራሴ ለሆኑት ጀፍ መርክሌይ እየደረሰ ያለውን የአማራ ህዝብ የዘር ማጥፋት ድርጊት በመረጃ በማስደገፍ ገለጻ ተደርጓል።

የአማራ ማህበር በኦሪገን የስራ አመራርና የቦርድ አባላትን እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚወክሉ 12 አባላት በአማራ ህዝብና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ በብልጽግናው መንግሰት እየደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት ድርጊት ለማሳወቅ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አጠናክረው በመቀጠል ጁን 30 ቀን 2026 ዓ.ም ለህዝብ እንደራሴው ጀፍ መርክሌይ ገለጻ አደርገዋል። የተሰጠው መግለጫ በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን የጅምላ ጭፍጨፋ፣ ግድያ፣ መፈናቀል፣ ከስራ መሰናበት፣ እገታ፣ ስደት፣ የጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና ፖለቲከኞች ያለ ፍርድ መታሰርን ያካተተ ነው። የመሰብሰብ፣ ሃሳብን በነጻነት የማራመድና የመያዝ መብት በአገዛዙ ስለመገደቡና ይህን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት በሀገሪቱ ህግ መሰረት ለማካሄድ በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና የህዝብ እንደራሴዎች ላይ አማራ በመሆናቸው ብቻ የዚህ መብት ተሳታፊ እንዳይሆኑ አገዛዙ የሚያደርገውን አምባገነናዊ ድርጊት በማስረጃ በማስደገፍ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

ገዳይ የሆነው የብልጽግና መንግስት የአማራ ነው ያለውን ባህል፣ እምነትና ታሪክ እንዴት እያጠፋ እንደሆነ በምስል ማስረጃ ተደግፎ ቀርቧል። የባህል መገለጫዎቹ፣ ቤተ እምነቶቹና ታሪካዊ ቅርሶቹ መውደማቸውን፣ በተለይ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከ100 ዓመታት በላይ እድሜ ያላቸውን አብያተ ክርስቲያናት ከእምነቱ ተከታዮቻቸው ጋር መቃጠላቸው ተገልጿል።

ከመጋቢት 2015 ዓም በክልሉ አገዛዙ ጦርነት ካወጀ ጊዜ ጀምሮ ከአራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መከልከላቸው፣ ት/ቤቶች በድሮንና በከባድ መሳሪያ በአገዛዙ መውደማቸው፣ ከውድመት የተረፉትም በወታደር ካምፕነት እያገለገሉ ስለመሆናቸው በመረጃ ተደግፎ ቀርቧል።

በተጨማሪም በክልሉ ያሉ የጤና ማዕከላት አገልግሎት እንደማይሰጡ፤ ህጻናት፣ እናቶችና አረጋውያን መታከም ከማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸውና በህክምና እጥረት በርካቶች ለሞት ስለመዳረጋቸው ገለጻ ተደርጓል።

አገዛዙ በሃሰተኛ ሪፖርት የውጭውን ዓለም እንደሚያጨበርብር፣ ወጣቱ ተስፋ የሌለው እንዲሆን እያደረገ እንደሆነና በሀገሪቱ ሃሳብን የመግለጽ፣ የመሰብሰብ፣ ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ መብትን የገደለና በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ እንዲህ አይነት ዜጎችን በሃይማኖትና በዘር እየከፋፈለ የሚጨርስ መንግስት እንዳላጋጠመ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

ይህንን ማለቂያ የሌለው አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ድርጊት እንዲቆም የህዝብ እንደራሴዎች ጫና በማድረግ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ፣

  • ⁠ ⁠በተለይም ደግሞ በአሜሪካ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውን House Resolution 937 እንዲጸድቅና እንዲተገበር ድጋፍ እንዲያደርጉ፣
  • ⁠ ⁠በአማራ ህዝብና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያጣራ ዓለም ዓቀፍ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን እንዲቋቋም ግፊት እንዲያደርጉ፣
  • ⁠ ⁠የአሜሪካ መንግሰትም ሆነ ሌሎች ዓለም ዓቀፍ አበዳሪ አካላት ለኢትዮጵያ መንግስት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጤ
  • ⁠ ⁠በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚካሄደው ጭፍጨፋ የገንዘብና የመሣሪያ ድጋፍ የሚያደርጉ ሀገራትን UAE, Turkye, Iran የመሳሰሉ ሀገራት የሚያደርጉትን የመሣሪያና የገንዘብ ድጋፍ እንዲያቆሙ ጫና እንዲደረግ ተጠይቋል።

የሴናተር ጀፍ መርክሌይ ጽ/ቤት ኃላፊዎች ሚትራ አኑሽራቫኒ እና ከሲካ ሽሮደር  በበኩላቸው በገለጻው በኢትዮጵያ በአማራና በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ በመንግስት እየተፈጸመ ያለውን አሰቃቂ ድርጊት ላይ በቂ ግንዛቤ እንዳገኙና በኦሪገን የሚኖረው የአማራ ህዝብም በምን ያህል ስቃይ ውስጥ እንዳለ ገልጸው ጽ/ቤታቸው ጉዳዩን በጥልቀት መርምሮ በምን መንገድ እገዛ እንደሚያደርግ ያሳውቃል ብለዋል። የአማራ ማህበር በኦሪገን የሚያደርገውን ማህበረሰብ ተኮር እንቅስቃሴዎች አጠናክሮ እንዲቀጥልና ማህበሩ በሚያደርጋቸው የማህበረሰብ አገልግሎት እንቅስቃሴዎች በመገኘት ድጋፍ እንደሚያደርጉ እንዲሁም ድምጹን ማሰማት እንዲችል በኦሪገን ግዛት በሚደረጉ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲወከል እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል። የማህበሩ የሥራ አስፈጻሚዎችና የሃይማኖት አባቶች በዝግጅቱ ላይ ተገኝተው ማብራሪያና ጥያቄ አቅርበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *