በምስራቅ አርሲ አማራንና የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነትን ትኩረት አድርገው በተፈፀሙ የማንነት ጥቃቶች ከ450 በላይ ንጹሓን ዜጎች መገደላቸውን ኢሰመጉ አስታወቀ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በምስራቅ አርሲ አማራንና የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነትን ትኩረት አድርገው በተፈፀሙ የማንነት ጥቃቶች ከ450 በላይ ንጹሓን ዜጎች መገደላቸውን ባወጣው ሪፖርት አስታወቀ።
ኢሰመጉ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ አርሲ ዞን በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች በተለይ በአማራና በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮችና ተቋማት ላይ በተፈፀሙ ጥቃቶች ቢያንስ 450 ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውን ምክር ቤቱ ባወጣው አዲስ ሪፖርት አስታውቋል።
ከመስከረም 2021 እስከ ሰኔ 2026 ባለው የምርመራ ጊዜ ውስጥ በተካተተው 158ኛው ልዩ መግለጫ ላይ፣ 37 ገጽ ያለው ሪፖርት አካላዊ ጉዳቶችን፣ የጅምላ እስራቶችን፣ አስገድዶ መድፈርንና በታጠቁ ቡድኖች የተፈፀሙ ሰፊ የንብረት ውድመትን ጨምሮ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በማስረጃ አስደግፎ በዝርዝር አቅርቧል።
ኢሰመጉ በምርመራው የአካል የመስክ ምልከታዎችንና የመረጃ አሰባሰብ መንገዶችን መጠቀሙን ገልጿል። በተጎዱት ዘጠኝ ወረዳዎች የተመዘገበው የሟቾች ቁጥርም እንደሚከተለው ነው፡-
- መርቲ፡ 117 ሰዎች
- ሼርካ፡ 116 ሰዎች
- ጄጁ፡ 101 ሰዎች
- ካባ፡ 47 ሰዎች
- ጉና፡ 26 ሰዎች
- ሆንኮሎ ዋቤ፡ 20 ሰዎች
- ሙኒሳ፡ 19 ሰዎች
- አሰኮ፡ 5 ሲቪሎችና 4 የአካባቢው ሚሊሻዎች
- የአርሲ አለቃ፡ 3 ሰዎች
መሆናቸውን ኢሰመጉ የሟቾችን ስምና ማንነት በሪፖርቱ ውስጥ አካቷል።
ከግድያዎቹ በተጨማሪ የታጠቁ ቡድኖች በሸርካ፣ ሮቤ፣ ጄጁ፣ መርቲና ሙኒሳ አካባቢዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን አፍነው ወስደዋል። አንዳንድ ተጎጂዎች ቤተሰቦች ከፍተኛ ገንዘብ ከከፈሉ በኋላ መፈታታቸውን አረጋግጠዋል፣ ሌሎች በርካቶች ደግሞ የት እንዳሉ፣ ብህይዎት ይኑሩ አይኑሩ እስካሁን አልታወቀም። በተጨማሪም ሪፖርቱ በጥቃቱ ወቅት አረጋውያን ዜጎችና ህጻናት ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው አጉልቶ ያሳያል።
እንደ ኢሰመጉ ገለጻ በምስራቅ አርሲ ያለው ደህንነት አሁንም እጅግ አደገኛ እንደሆነ አስጠንቅቋል። በዚህ ዘርንና ሃይማኖትን ትኩረት አድርጎ እየተፈጸመ ባለው ግድያ ከ14,000 በላይ ዜጎችን ህይወታቸውን ለማትረፍ አካባቢያቸውን ለቀው ተሰደዋል።የተፈናቃዮች ስብጥርም
- ጄጁ፡ 6,216 ዜጎች
- ሼርካ፡ 3,746 ዜጎች
- አሰኮ፡ 2,133 ዜጎች
- ካባ፡ 1,270 ዜጎች
- መርቲ፡ 1,036 ዜጎች
- ሙኒሳ፡ 29 ዜጎች
- ጉና፡ 21 ዜጎች መፈናቀላቸውን ኢሰመጉ በሪፖርቱ ዘርዝሯል።
ጥቃቶቹ የሃይማኖት ተቋማትንም ኢላማ ያደረጉ ሲሆን፣ ለዘመናት የቆዩ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣ ተዘርፈዋል ወይም እንዲዘጉ መደረጋቸው ተገልጿል።
የኢሰመጉ የተሰነዱ ድርጊቶች መሰረታዊ ህገ-መንግስታዊ መብቶችንና ዓለም አቀፍ የህግ ደረጃዎችን የሚጥሱና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ምልክቶች የያዘ ነው ሲል ደምድሟል። በዚህም ምክንያት ምክር ቤቱ ለፌዴራልና ለክልል ባለስልጣናት በአስቸኳይ እንዲተገበሩ የሚከተለውን ጥሪ አቅርቧል፡-
- ለተጋላጭ ማህበረሰቦች ዘላቂ የደህንነት ጥበቃ እንዲደረግ።
- በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉ ወንጀለኞችን መርምረው ለፍርድ እንዲያቀርቡ።
- ለተጎጂዎች በቂ ካሳ እንዲሰጥና የተፈናቀሉ ቤተሰቦች ወደ ቤታቸው በሰላም እንዲመለሱ እንዲመቻች ጠይቋል።
የፌዴራልም ሆነ የክልል የደህንነት ባለስልጣናት ኢሰመጉ ግኝቶችን በሚያጠናቅርበት ወቅት መደበኛ ምላሽ ለመስጥት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ አስታውቋል።
የፌዴራልም ሆነ የኦሮሚያ የአስተዳደር መንግስታት ጥቃቶቹን ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (OLA) ጋር በተደጋጋሚ እንደሚያይዙት ይገልጽና ድርጅቶች ግን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በ2010 ዓ.ም ስልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በክልሉ በስፋት የሚንቀሳቀስ በመሆኑ የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት የመንግስት መሆኑን ጠቅሷል። በተለያዩ ጊዜያት መንግስት ከኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ድጋፍ ያገኘ ሲሆን ምክር ቤቱ ጥቃቶቹ የየትኛውንም ሃይማኖት ተከታዮች ኢላማ አላደረጉም ብለው ሪፖርት ማድረጋቸውን ጠቅሷል።
ይሁን እንጂ በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ በሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ ዋዜማ፣ በአርሲ በሸርካ፣ በአርሲ የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ የተፈፀመ ሰፊ ጥቃት፣ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ የቆየ ቤተክርስቲያን ከመቃጠሉም በላይ በደርዘን የሚቆጠሩ የእምነቱ ተካታዮችን ለሞት እንደዳረገ ባደረገው ምርመራ ማረጋገጡን አስታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፓርላማ ላይ ቀርበው ጥቃቱ “ምርጫውን ለማደናቀፍ የተነደፈ” ሴራ እንደሆነ መናገራቸውንም ኢሰመጉ ባወጣው ሪፖርት አስታውሷል።
ኢሰመጉ ለረጅም ዐመታት በኦሮሚያ ክልልና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን እያጋለጠ ያለ ገለልተኛ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድረጅት ነው።
