አማራን ለምን?

በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመው ግፍ፣ መፈናቀል እና ጭፍጨፋ በዋነኛነት ከስርዓታዊ የፖሊሲ ልዩነቶች፣ ከመንግስት ኃይሎችና ታጣቂዎች መካከል ከሚካሄደው ከባድ የትጥቅ ግጭት፣ እንዲሁም ብሔር ተኮር ኢላማ ከሚያደርጉ ጥቃቶችና የተጠያቂነት መጥፋት የሚመነጩ ውስብስብ የሰብአዊ መብት ቀውሶች ናቸው።

እንደ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንንም ይጨምራል) ሪፖርቶች፣ በጥቃቶቹ እና በግፉ መከሰት ላይ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡-

  1. የኦነግ፣ የሻቢያና የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅቶች የፈጠሩት አሉታዊ ትርክት

ኦነግ (የኦሮሞ ነፃነት ግንባር) እ.ኤ.አ በ 1973 በኦሮሞ ብሔርተኞች የተመሰረተ የፖለቲካ ድርጅት ነው ሲሆን ዓላማውም የኦሮሞ ሕዝብ ራሱን በራሱ በነፃነት የማስተዳደር መብት እንዲያረጋግጥ እና ከጭቆና ነፃ ለማውጣት በሚል ዓላማ ነው። ህወሓት (የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ) በበኩሉ የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. የካቲት 18 ቀን 1975) በትግራይ ክልል ዴደቢት በረሃ የትጥቅ ትግሉን በመጀመር  የተመሠረተና ዓላማውም በወቅቱ የነበረውን የደርግ ወታደራዊ መንግሥት ጭቆና በመቃወም እና የትግራይን ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ለማረጋገጥ የሚል ነበር። ከላይ ለተገለጹት እንደ እንጀራ አባት የሚቆጠረው የኤርትራ ህዝባዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ሻቢያ) ደግሞ በ1970 እ.ኤ.አ ከጀብሃ በመገንጠል ተመስርቷል። ከጀብሃ ጋር በተፈጠረ የፖለቲካ እና የአደረጃጀት ልዩነት በመገንጠል የተፈጠረ ነው። ኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ ሌሎች የጀብሃ ታጋዮችና ምሁራን በመነጠል፣ በኋላ ላይ ማርክሲስት-ሌኒኒስት ርዕዮተ ዓለምን በመከተል ሰፋ ያለ ህዝባዊ መሰረት የፈጠሩበት ንቅናቄ ነበር።

የሶስቱም ድርጅቶች ዓላማ ተመሳሳይ ነው። ህዝባችን የሚሉትን ከኢትዮጵያ መገንጠልና የራስን አስተዳደር መመስረት ነው። ለዚህ ግባቸው ደግሞ መስዋዕት አድርገው ያቀረቡት የኦርቶዶክስ እምነትንና የአማራን ህዝብ ነው። አማራውን ጨቋኝ ፣ ወራሪ፣ ቀኝ ገዥ፣ ነፍጠኛ፤ ኦርቶዶክስን ደግሞ የእድገት ጸር፣ ወግ አጥባቂ፣ ኋላ ቀር ወዘተ እያሉ ትርክቶችን መስራት ጀመሩ። ይህን ትርክት ለ60 ዓመታት ያህል የፖለቲካቸው ማስፈጸሚያ በማድረግ ቀጠሉበት። አማራ የሚመስሉ ሰዎችን አጋር በማድረግ ለአማራው ለራሱ ይነግሩት ጀመሩ። የሚገርመው የትግራይና የአማራ ህዝብ ሰርቶ አደር በመሆኑ መልካም እድል ባለባቸው አካባቢ ሁሉ በመሄድ ለራሱም ለሀገሩ ብዙ ደክመዋል። ይሁን እንጂ ወራሪና ነፍጠኛ የሚለውን ትርክት ለአማራ ብቻ በመስጠት በአማራ ህዝብ ላይ ሌሎች ቤሔረሰቦች በተለይም አብዛኛው የኦሮሞ ህዝብ ጥላቻ እንዲያድርበትና እርምጃ እንዲወስድ አድረጎታል። በዚህ ትርክት የተነሳ አማራና ኦርቶዶክስ እስካሁን ድረስ በጅምላ ይገደላሉ፣ ይፈናቀላሉ፣ ቤተ እምነቶችና መኖሪያ ቀያቸው ይቃጠላል፣ ጀሮን ጭው አይንም የሚጋርዱ ግፎች እየተፈጸሙበት ይገኛል። የሚገርመው ነገር ብልጽግና ወደ ስልጣን ሲመጣ ከዚህ ስሁት ትርክት ሊያወጣን በሚል ምንም ሳይሰራ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ደገፈው። ነገር ግን ወርቅ ላበደረ ጠጠር እንዲሉ ግፎች ከአሁን ቀደሞች በከፋ ቀጥሏል።

  1. ብሔር ተኮር ጥቃቶችና መፈናቀል፡ በብሔር ዘውግ ሀገሪቱን የሚገዙ አካላት በመጡ ቁጥር ግፍ የሚፈጸምበት የአማራ ህዝብ ነው። በዚህም የተነሳ በክልሉ ውስጥና ከክልሉ ውጭ በሌሎች የሀገሪቱ አስተዳደር ክፍሎች በተለይን እንደ ኦሮሚያ ክልል ባሉ ውስጥ የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች በታጠቁ ኃይሎች ሆን ተብለው ኢላማ የተደረጉ ጭፍጨፋዎችና የንብረት ውድመት እየደረሰባቸው መሆኑን የመንግስት ተቋም የሆነው ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሪፖርቶች ሳይቀሩ ያመለክታሉ።
  2. የፖለቲካ፣ የአስተዳደር አለመግባባቶችና የትጥቅ ግጭቶች፡ ከድሮም ጀምሮ የአካባቢ አስተዳደሮች በተለያዩ ምክንያቶች ግጭቶች ቢኖሩም እንዳሁኑ ግን የከፋ ግጭት አጋጥሞ አያውቅም። መነሻ የሆነውም የብልጽግናው መንግስት የክልሉን ልዩ ኃይል በትግራይ ጦርነት ውስጥ ከተጠቀመበት በኋላ አስቀድሞ ላቀደው ክልሉን እንደ ትግራይ የማድረግ ጉዞ መሰናክል እንዳይሆን እንዲፈርስ በመድረጉና በዚህ ውሳኔ ያልተስማሙ የአማራ ፋኖን በመመስረት የትጥቅ ትግል ጀመሩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ክልሉ በድሮን፣ በተዋጊ አውሮፕላኖች፣ በከባድ መሳሪያዎችና በታጣቂዎች መከራውን እያየ ይገኛል። ከብልጽግና በፊት ቢያንስ በክልሉ ጅምላ ጭፍጨፋ አይካሄድበትም ነበር። አሁን አማራ እያለቀ ያለው ቤበቱና በቀየው ነው። ለወትሮው የሀገር መከላከያ የሀገርን ሉዓላዊነት ነበር የሚያስከብረው አሁን ግን የራሱን ዜጎች በተለይም አማራን በማጥፋት ላይ ዘመቻ እያካሄደ ይገኛል። ከትጥቅ ትግሉ ጋር ቀጥታ ግንኙነት የሌላቸው ንጹሃን ዜጎች መኖሪያና ተቋማት በመከላከያው እንዲወድሙ በመደረጉ በርካታ ሲቪሎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ አካል ጉዳተኛ ሆነዋል። ይህን ጉዳይ አስመልክቶ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (UN) እና Human Rights Watch ድርጊቱን በማውገዝ በተለያዩ ጊዜያት መግለጫ እንዲያወጡ አስገድዷል።
  3. የተጠያቂነት መጥፋት፡ በጅምላ ጭፍጨፋ፣ በከባድ የሰብአዊ መብት ረገጣ (እንደ ግድያ፣ ዝርፊያ እና ጾታዊ ጥቃት ያሉ)ና በጦር ወንጀሎች የተሳተፉ አካላት በህግ ፊት አለመቅረባቸው ለግፉ መቀጠል ዋና ምክንያት ሆኗል። የ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪዎችን ጨምሮ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ለኢትዮጵያ መንግስት ግፊት እንዲያደርጉ እየተጠየቀም ይገኛል። ተጠያቂነትን ለማምጣት መሪዎች ፍላጎት የላቸውም ምክንያቱም እልቂቱን እንዲፈጽሙ የሚያዘጋጇቸውና ድጋፍ የሚያደርጉላቸው የመንግስት አካላት በመሆናቸው። በቅርቡ የተጋለጠው ኮረ ነጌኛና 120 ቡድን የተባሉ ገዳይ ቡድኖች የተቋቋሙት በጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ ነው። እነዚህ ቡድኖች በዋናነት ትኩረታቸው በአማራና በኦርቶዶክስ እምነት ላይ ቢሆንም ለአብይ ስጋት ናቸው የተባሉ አካላትንም ይጠልፋሉ፣ ይሰውራሉ፣ ይገላሉ፣ ንብረታቸውን ይወርሳሉ። በዚህ መንገድ የተቋቋሙ ገዳዮችን መንግስት ራሱ የፈጠራቸው በመሆኑ እንዴት ሊጠይቃቸው ይችላል።
  4. ለውድቀታቸው የአማራን ህዝብ እንደ ምክንያት ማቅረብ፡ ክልል መሰረትን ካሉ በኋላ እንኳን ልማትና ዲሞክራሲ ማስፈን ሲያቅታቸው ኢኮኖሚውንና ፖለቲካውን አማራ ስለያዘው ነው ብሎ ማላከክና ከኢኮኖሚውም ከፖለቲካውም ማፈናቀል ሥራን መሥራት። በአሁኑ ሰዓት አማራ በፖለቲካው ባይተዋር፣ በኢኮኖሚው ደግሞ ተሳዳጅና ተወራሽ ነው።
  5. የስነ ልቦና ችግሮች፡ የኦሮሞም ሆነ የትግራይ ልሂቃን ፖለቲከኞች ሥልጣኑን ይዘውም እንኳን ቢሆን አማራንም እየመራን ብለው ለማመን በስነ ልቦና ዝግጁ አለመሆናቸው። በዚህም የተነሳ መሳሪያ ያነሳውንም ያላነሳውንም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያጠፉታል። እንዲህ አይነቱ የበታችነት ስነ ልቦና እስካልጠፋ ድረስ ችግሩ በቀላሉ የሚቀረፍ አይመስልም።
  6. የቀኘ ገዥዎች አስተምሮ፡ ከፖርቹጋል ሚሽኔሪዎች ጀምሮ የተጀመረው ቀኝ የመግዛት ሙከራዎች ትተውት ያለፏቸው አስተምህሮቶችና ትርክቶች በአማራና በኦርቶዶክስ እምነት ላይ ነበር። በኋላም እንግሊዞች፣ ቀጥለውም ጣሊያኖች፣ ኦቶማኖች፣ መሃዲስቶች ወዘተ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ሁሉም በሽንፈት ተመልሰዋል። በእነዚህ የሙከራ ጊዜያቶች ለሽንፈቶቻቸው እንደ ምክንያት የሰጡት አማራንና ኦርቶዶክስን ነው። አማራ ሀገሬን አላስደፍርም በማለቱ የኦርቶዶክስ ልሂቃን ደግሞ የካቶሊክና የፕሮቴስታንት እምነቶችን ስነ መለኮታዊ አስተምህሮ በክርክር ሳይቀር በመርታት ስለ አሳፈሯቸው ነው። በመሆኑም በመጽሐፎቻቸው ሳይቀር ኢትዮጵያን ለመግዛት አማራንና የኦርቶዶክስ እምነትን ከተቻለ ማጥፋት ካለያም ማዳከም ያስፈልጋል ብለው ጽፈዋል። አማራ የሌሎች በሔሮች ጨቋኝ ብለው አስተምረዋል። ይህን ትርክትም የኢትዮጵያ ብሔርተኛ መሪዎች ሀገሪቱን ለመምራትና ያለ ተጠይቆ ሃብቷን ለመዝረፍ ሁለቱን ተቋማትን በጠላትነት ፈርጀው ለማትፋት እየሰሩ ይገኛሉ።

 እነዚህና በሌሎች ምክንያት የአማራ ህዝብ ከመቸውም ጊዜ በባሰ በህልውና ፈተና ውስጥ ይገኛል። በመሆኑም የራሱን ህልውና የማረጋገጥ ሥራውን ቅድሚያ ሰጥቶ በአንድነት በመሥራት ሁሉን ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የምታስተናግድና መድን የምትሰጥ ኢትዮጵያን መገንባት ያስፈልጋል። በተለይም የችግሩ ምንጭ ከሆኑት ምዕራባውያን መፍትሔ ለማግኘት መሞከሩ ብዙ ተስፋ የሚሰጥ አይሆንም። ይልቁንም የራስን ኃይልና ሃብት አስተባብሮ ራስን ነጸ ማውጣት ያስፈልጋል። ጉልበት ሲኖርህ ሁሉም ወደ አንተ ይመጣሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *