በዋግኽምራ ዞን በድርቅ ምክንያት ከ4 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተሰደዱ
በዋግኽምራ ዞን በድርቅ ምክንያት ከ4 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተሰደዱ
አንዳንዶች ልጆቻቸውን ለልመና እያሰማሩ መሆኑ ተገልጧል
ህጻናትን ለልመና የሚያሰማሩ አካላት ላይ መንግስት ጥብቅና ሕጋዊ ርምጃ ለመውሰድ የዞን ግብረ ኃይል ማደራጀቱን ዐሳውቋል
በአማራ ክልል በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን፣ ፃግብጂ ወረዳ በሚገኙ አራት ቀበሌዎች በተከሰተ ድርቅ ምክንያት ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች ቀዬያቸውን ጥለው ወደ ተለያዩ ከተሞች መሰደዳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎችና መምህራን ገለጹ። በርካታ ህጻናት ትምህርታቸውን አቋርጠው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ደሴና ሌሎች ከተሞች በመሰደድ በልመና ተግባር ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙም ተገልጧል ።
በደሴ ከተማ በልመና ላይ የሚገኙ የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች፦ ስደቱ የተከሰተው በአካባቢያቸው የሚበላ ነገር በመጥፋቱና በድርቁ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። መምህራን በበኩላቸው ስደቱ በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ገልጸው፣ አንዳንዶች ልመናን እንደ ገቢ ምንጭ በመጠቀም ልጆቻቸውን ለልመና እያሰማሩ መሆኑንም ተናግረዋል ።
የዞኑ አደጋ መከላከልና ሥራ አመራር ኮሚሽን በበጋው ወቅት ሰብላቸው ለተጎዳባቸው 27 ሺህ ሰዎች የምግብና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል። የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ምህረት መላኩ እንደገለጹት፦ በትክክል በችግር ምክንያት የተሰደዱትን ነዋሪዎች ወደ ቀዬያቸው በመመለስ ድጋፍ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጠዋል፥ በተቃራኒው ግን “ልመናን እንደ ልማድና እንደ ተጨማሪ ገቢ ምንጭ” የሚጠቀሙና ህጻናትን ለልመና የሚያሰማሩ አካላት ላይ መንግስት ጥብቅና ሕጋዊ ርምጃ ለመውሰድ የዞን ግብረ ኃይል ማደራጀቱንም ዐሳውውቀዋል።ሲል የዘገበው የደሴው ወኪላችን ኢሳያስ ገላው ነው። በዜና መፅሄት ዝግጅት ዝርዝር መረጃ ይኖረናል።
ዘገባው የDW ነው።
