ማህበሩን ለማጠናከር ውይይት ተካሔደ
በኦሪገንና ዋሽንግተን ቫንኮበር የአማራ ማህበር ሥራ አመራሮች ማህበሩን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሄዱ።
(ኦሪገን፣ 3/15/2026) በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ሁሉን አቀፍ የሰብአዊ ቀውስ ላይ የአማራ ተወላጆች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ለማስቻል እየተሰራ ነው። በኦሪገን ሀገረ ግዛት ውስጥ በርካታ የአማራ ተወላጆችና ደጋፊዎች ይኑሩ እንጂ በአንድነት ተሰባስበው አስተዋጽኦ ከማድረግ አንጻር ብዙ እንደሚቀር ተወያይተዋል። ይህንን የዝምታ አካሄድ ለመስበርና ለማሰባሰብ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም አባላቱን ለማሰባሰብ በጥንካሬ ለመስራት ተወያይተዋል።
በኦሪገንና ዋሽንግተን ቫንኮበር ግዛት ውስጥ የሚኖሩ አማራዎችንና ደጋፊዎችን በመለየት በአካል፣ በስልክና በሌሎች የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም ማህበሩ እስካሁን ያደረጋቸውን የሰብአዊ ድጋፎችና የመሳሰሉ ስራዎችን በማስረዳት ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ቢያደርግ ደግሞ የበለጠ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ግንዛቤ በመፍጠር አባላቱን የማሰባሰብና የማስፋት ስራዎችን አጠናክረው ለመስራት አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ሀገር ቤት ያለውን የአማራ ክልል ነባራዊ ሁኔታና የሰብአዊ አያያዝ በተመለከተ በቦታው የሚገኙ የፋኖ አመራሮችን በመጋበዝ ለአባላቱ ማብራርያ እንዲሰጡ ለማድረግ እንዲሰራ ወስነዋል።
የአማራ ህዝብ በዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ ያለ መሆኑን መረዳት አስፈላጊ መሆኑን የተነጋገሩ ሲሆን በኦሪገን የሚኖሩ ሁሉ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ተደርጓል። የዚህ ታላቅ ህዝብ ልጆች በአማራ ላይ እየደረሰ ያለውን የሰብአዊ ቀውስ ለመመከት የበኩላቸውን በመወጣት ታላቅ ሥራ እንዲሰሩ አመራሩ ጥሪ አቅርበዋል።
