ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ (አባ ታጠቅ) ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ
ጀግናዉ ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ (ጥር ፮ ቀን ፲፰፻፲፩ ዓ.ም. እስከ ሚያዝያ ፮ ቀን፲፰፻፷ ዓ.ም.) ከ፲፰፻፵፯ ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞታችው ድረስ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነበሩ። በትውልድ ስማቸው ካሳ ኀይሉ ሲባሉ፣ በፈረስ ስማቸው አባ ታጠቅ፣ በወታደራዊ ስማቸው መይሳው ካሳና እንዲሁም አንድ ለናቱ ተብለው የሚታወቁ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ወታደርና ፖለቲከኛ ነበሩ። ቴዎድሮስ ጥር ፮ ቀን ፲፰፻፲፩ ዓ.ም. ሻርጌ በተባለ ቦታ ቋራ ውስጥ፣ ከጎንደር ከተማ በስተ ምዕራብ ተወለዱ። የተወለዱትም አገሪቷ በባላባቶች ተከፋፍላ በምትመራበት-ዘመነ መሳፍንት በሚባለው ወቅት ነበር። አባታቸው ደጃዝማች ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ የቋራ ገዢ ነበሩ። ዓፄ ቴዎድሮስ በህጻንነታቸው የቄስ ትምህርት ከቀሰሙ በኋላ፣ የአጎታቸውንና በኋላም ለጥቂት ጊዜ የጎጃሙን ጦር መሪ የጎሹ ዘውዴን ጦር ተቀላቀሉ። በዚሁ የውትድርና ዘመናቸው ከፍተኛ ችሎታን ማስመዝገብ ስለጀመሩና ዝናቸው ስለተስፋፋ በ፲፰፻፴፱ ዓ.ም. በወይዘሮ መነን ሊበን አምዴ አነሳሽነት የልጇን የራስ አሊ አሉላን ልጅ፣ ተዋበች አሊን አገቡ፤ እንዲሁም በደጃዝማችነት ማዕረግ የቋራ አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ። ቴዎድሮስ ግን በ፲፰፻፵፬ ዓ.ም. አጠቃላይ የዘመነ መሳፍንት ሥርዓትን በመቃወም በሰሜናዊ ባላባቶች ላይ ዘመቻ ጀመሩ። በተከታታይ ዘመቻወች የገጠሟቸውን ባላባቶች ስላሸነፉ፣ መጀመሪያ የራስ ማዕረግን በኋላም የንጉሥ ማዕረግን በአንድ ዓመት ውስጥ ተቀዳጁ። በየጊዜው በሚያደርጉት የተሳካ ዘመቻ የዘመኑን ባላባቶች ኃይል በመሰባበር የካቲት ፫ ቀን ፲፰፻፵፯ ዓ.ም ንጉሥ ካሳ - ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ተብለው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆኑ። ሥርዓተ ንግሡ...Read More
