ለሰብአዊነት ቅድሚያ ይሰጣል

ፖርትላንድ፡ሚያዚያ 9 ቀን 2018 ዓ.ም

የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን)ወደ አንድነት መምጣቱ ለሰብአዊነት የሚሰጠውን ትኩረት ከፍ አድርጎታል ሲሉ የድርጅቱ አመራሮች ገለጹ።

ይህ የተገለጸው  የአማራ ማህበር በኦሪገን በአማራ ክልል ሰብአዊ ቀውስን ለመቀነስ ንቅናቄው ምን እየሰራ እንደሆነ ተጠይቆ ለተሰብሳቢዎቹ አመራሮች ማብራሪያ በሰጡበት ስብሰባ ላይ ነው። ንቅናቄው ዓለም ዓቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን አክብሮ የሚሰራ መሆኑም ተረጋግጧል። በቅድሚያ ማብራሪያ የሰጡት የአፋብን ህዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ አርበኛ አስረስ ማረ ሲሆኑ በማብራሪያቸውም ፋኖ የህብረተሰቡ ጥያቄ የነበረውን የአንድነት ጉዳይ በድል ካጠናቀቀ ጊዜ አንስቶ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ አደጋዎች ሰዎች እንዳይጎዱ ቀጥታ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ችግሩን ለሚመለከታቸው አካላት በማድረስና እርዳታ እንዲደርሳቸው በማድረግ በኩል የተሻለ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ድርጅቱም በተመሰረተ በአጭር ጊዜ በርካታ ውሳኔዎችንና ትላልቅ ወታደራዊ ድሎች አስመዝግቧል። ይሁን እንጂ ድርጅቱ ዲያስፖራውን በማደራጀት እና ተገቢው ድጋፍ እንዲደረግ በማድረግ በኩል ብዙ ይቀራል ብለዋል። አገዛዙ ውጊያ ተዋግቶ ያሸነፈበት፣ የተረጋጋ አስተዳደራዊ መዋቅር ዘርግቶ መስራት እንዳይችል ከመደረጉም በላይ ትጥቅና ሥንቅ ከጠላቶቻችን በሚል መርህ ወታደራዊ ትግሎችን በማከናዎን ሁሉንም በድል በማጠናቀቅ ከፍተኛ የሆነ ትጥቅና ስንቅ መገኘቱም በላይ አገዛዙ ንጹሃን ላይ ግፍ ከመፈጸም ባለፈ ከፋኖ ጋር ተዋግቶ ድል ያደረገበት ዐውደ ውጊያ እንደሌለም አርበኛ አስረስ አብራርተዋል።

“ፋኖ እንቅስቃሴ እንደጀመረ ዲያስፖራው አገዛዙ የሚፈጽማቸውን የጦር ወንጀሎች ለዓለም በማሳወቅና ድጋፎችን በማድረግ ብዙ ሥራዎች የተሰሩ ሲሆን መሃል ላይ በነበረው የፋኖ ክፍፍል የተነሳ መቀዛቀዝ አሳይቷል፡ አሁን በአፋብን መመስረት ማግስት እንደገና የመነቃቃት ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፤ የዚህ ማሳያው ደግሞ በአሜሪካ የሚገኙ 36 ማህበራት በጋራ ለመስራት ስምምነት መድረሳቸው ነው” ያሉት ደግሞ የአፋብን የውጭ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊው አርበኛ ብሩክ ስለሺ ናቸው።

አፋብን በአጭር ጊዜ ውስጥ ህዝብን አስተባብሮ የአገዛዙን የውሸት ምርጫ በሰላማዊ ሰልፍ እንዲያወግዙ ማድረግ መቻሉንም አርበኛ ብሩክ አክለው ገልጸዋል። ነጻ የውጡ አካባቢዎችን አስተዳደራዊ መዋቅር በመዘርጋት ፍትህን የማስፈን ሥራ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አርበኛ ብሩክ በዲያስፖራው በኩል ያለውን የእውቀትና የሃብት ካፒታል ለመጠቀም አጠናክረው እንደሚሰሩ አብራርተዋል። አክለውም ዲያስፖራው መረጃን ለዓለማቀፍ ህብረተሰብ በማድረስ ከፍተኛ የሆነ የዲፕሎማሲ ሥራ በመስራት የበኩልን ታሪካዊ ኃላፊነት እንዲወጣና ተጽእኖ ፈጣሪ እንዲሆን አሳስበዋል።

አፋብን ፍትሃዊ ባልሆነ ምርጫ ማንም እንዳይሳተፍ ባወጣው ማስጠንቀቂያ መሰረት ብዙዎቹ ስራውን እየተው መሆንና አገዛዙም በአማራ ክልል ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል በመረዳቱ በወታደራዊ ጀኔራሎች ዘመቻ እያካሄደ ህብረተሰቡ በግዳጅ የምርጫ ካርድ እንዲያወጣ ካስደረጉ በኋላ ካርዱን ሰብስበው ይዘው ይሄዳሉ። ይህንን የሚያደርጉት ደግሞ ከቢሯቸው ቁጭ ብለው በተመዘገበው ሰው ልክ የድምጽ መስጫ ካርደ በምርጫ ኮረጆ ለመክተት በማሰባቸው ነው ያሉት ደግሞ የአፋብን የአጋርነትና ትብብርና ምመሪያ ኃላፊው አርበኛ አበበ ፋንታው ናቸው። የመንግስት መዋቅር በክልሉ የለም። መሬት ላይ የሚከናዎን ሥራ የለም። መንግስት አለሁ እያለ ያለው በሚዲያ ፕሮፖጋንዳ ብቻ መሆኑንም አርበኛ አበበ አክለው አስረድተዋል።

በክልሉ ያሉ ሌሎች ብሔሮች ብቻ ሳይሆን በመላው ሀገሪቱ የሚገኙትም እጣ ፈንታቸው ተመሳሳይ ስለሆነ የትግሉ አጋዦች እንጂ አደናቃፊዎች ሊሆኑ አይችሉም ያሉት አርበኛ አስረስ አፋብን ካለው የአደረጃጀት ግዙፍነት አንጻር በሌሎች ድርጅቶች ሊጠለፍ የሚችልበት መንገድ የለም። ሌሎች ድርጅቶችም ወደ እኛ ይመጡ ካልሆነ በቀር አፋብን ወደ እነሱ የሚሄድበት ደረጃ ላይ አይደለም ሲሉም አክለዋል። በአንዳንድ አካላት የሚነሱ ብዥታዎችም በመንግስት ሚዲያ ፕሮፖጋንዳ የተፈጠሩ እንጂ እውነታ የላቸውም። በመሆኑም አፋብንን የማጥላላትን የአገዛዙን ፖሮፖጋንዳ በመግዛት ህብረተሰቡ እንዳይጠለፍ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ሲሉም አርበኛ አስረስ አሳስበዋል።

አፋብን ግዙፍ ጦር ያለው፣ ልምድ ባላቸው ጠንካራ አመራሮች የሚመራ፣ ሰለቸኝ ሳይል በስንቅም በትግልም የሚደግፈው ሰፊ ህዝብ ያለው፣ የግል ጥቅሙን ትቶ ለህዝብ ህልውና ህይወቱን የሰጠ የተማረ ታጋይ ያለው ድርጅት በመሆኑ በማንም፣ በምንም፣ መቼም ቢሆን ሊኮላሽና ሊጠለፍ የሚችል ትግል አለመሆኑን ሁሉም አመራሮች በአጽንኦት ለተሰብሳቢዎች ገልጸዋል። የህልውና ጥያቄ ይዞ ትግል የገባ ድርጅት ህልውናው እንዲጠፋ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ለሰሩበት አካላት ትግሉን አሳልፎ ይሰጣል ብሎ ማሰብ ጸሐይ በምዕራብ ትወጣለች ብሎ እንደማሰብ መሆኑን በአጽንኦት ተገልጿል። በመሆኑም በውጭ ያለው የአማራ ህዝብ የህልውና ትግል አስመልክቶ በዲፕሎማሲ፣ በሰብአዊ ድጋፍ፣ በእውቀትና በሃብት አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል የአፋብን አመራሮች።

የአማራ ትግል በቅድሚያ ለአማራ ህዝብ ማህበራዊ ፍትህን ማስፈንና ለደረሰበት በደልም የካሳ ጥያቄ ማቅረብ መሆኑን ገልጸው ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ በተናበበና በተቀናጀ መልኩ ትግሉን በመምራት የአማራን ህልውና ማረጋገጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ተሳታፊ የነበረው የኦሪገን እና ቫንኮበር ዋሽንግተን አማራ ማህበር አባላት አርበኞቹ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሁነው ማብራሪያ ለመስጠት በመቻላቸው እጅግ ደስተኛ እንደሆኑ እና በቀጥታ መሬት ላይ ያለውን እውነታ በመስማታቸው ይበልጥ አንድነትን እና ተነሳሽነትን እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል። ከዚህም በመነሳት በለቱ ለተጎዱ ወገኖቻችን የሚውል ወደ $3350 የለገሱ ሲሆን ወደፊትም የሚያደርጉትን ሰብአዊ ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *