በኦሮምያ አርሲ ዞን የደረሰውን ጭፍጨፋ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
ከኦሪገን አማራ ማህበር የተሰጠ መግለጫ
በኦሮምያ አርሲ ዞን በንጹሃን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ከስርዓቱ ገዳይነት ባህሪይው የመነጨ በመሆኑ ሁሉም የሰው ልጆች ሊያወግዙትና ሊታገሉት የሚገባ ጉዳይ ነው። ይህ የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴ እንደ በፊቶቹ ጭፍጨፋዎች ሁሉ በራሱ በአገዛዙ የተዘጋጁና የተፈጸሙ መሆናቸውን በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ለዚህም ዋነኛ ማስረጃው ያለምንም ማጣራት የአገዛዙ አፈቀላጤ ሃይሉ አዱኛ ወጥቶ “ኦነግ ሸኔ ፈጸመው” ማለቱና በቀጣይ ቀን ደግሞ “ድርጊቱን የሚያጣራ ልዑክ እልካለሁ” ማለቱ፤ እንዲሁም የአገዛዙ የፕሮፖጋንዳ ሚዲያዎች ከድርጊቱ በፊት ሰብስቦ ምርጫውን ለማደናቀፍ በሃይማኖት ተቋማትና በተከታዮቻቸው ላይ ጥቃት ሊፈጸም ስለሚችል ጉዳዩን እንዳትዘግቡ የሚል አቅጣጫ መስጠቱ ድርጊቱ በዕቅድ ስለመፈጸሙ ማረጋገጫዎች ናቸው።
ይህ አረመኔ ገዳይ መንግስት ከመጣ ጊዜ አንስቶ ስንት የአማራ ልጆች ታረዱ፣ ከእነነፍሳቸው በቤታቸው ተቆልፎባቸው ተቃጠሉ፣ ስንቶች በህይዎት ወደ ጥልቅ ጉድጓድ ተጣሉ፣ ስንቶች ቀባሪ አጥተው ለጅብና ለአሞራ ተዳረጉ፣ ስንት አብያተ ክርስቲያናት ተቃጠሉ፣ ስንት ንብረት ወደመ ተዘረፈ፣ ስንት ህዝብ ያለማውን ቀየ ትቶ በአማራነቱ ተሳደደ? ለዚህ ማን ምን አደረገ? መልሱ ምንም ከማይፈይድ መግለጫ በቀር ምንም ነው።
እረኛ ተብለው በጴጥሮስና ጳውሎስ የተሰየሙት የቤተ ክርስቲያኗ መሪዎች፤ ምዕመኑ የበጉ ምሳሌዎች ክረስቲያኖች ሲታረዱ፣ ስለእምነታቸው ሲቃጠሉ ዓለማዊ ምቾታቸውን መርጠው ዝምታን መምረጣቸው ችግሩን የከፋ ከማድረጉም በላይ እነሱም ከገዳዮች እኩል ማሰለፋቸውን ያሳያል። በዚህም ከሊቀ ካህኑ ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉትን መለኮታዊ አደራ አልተወጡምና አገልገሎታቸው በምዕመኑ ዘንድ እምነት እያጣ እንዲሄድ አድርገዋል። በጎች እረኛቸው ከተኩላ ካልጠበቃቸው እራሳቸውን በማደራጀት እረኛውንም ቀበሮውንም መታገልና የራስን ህልውና ማረጋገጥ የግድ ከሚልበት ደረጃ የተደርሷል። ውሃ ከማይቋጥር መግለጫም መውጣት የግድ ከሚሆንበት ደረጃ ላይ መደረሱን ማህበራችን በጽኑ ያምናል።
በመሆኑም የኦሪገን የአማራ ማህበር
- የዘር ማጥፋት ድርጊቱ በአገዛዙ አደራጅነትና ጠንሳሽነት የተፈጸመ መሆኑን ይገነዛባል፣ አምርሮም ይቃወማል
- እስካሁን በአርሲ፣ በወለጋ፣ በጅማና በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጸሙ የዘር ማጥፋት ድርጊቶች ፍትህ እንዲያገኙ ወይም እርምት እንዲወሰድ በአገዛዙም ሆነ በእምነቱ መሪዎች የተወሰደ እርምጃ ባለመኖሩ ወደፊትም ላለመቀጠሉ ዋስትና ስለሌለ ምዕመኑ ራሱን ለመከላከል የሚያደርገውን ማንኛውንም እንቅስቃሴ ማህበራችን ይደግፋል፣
- በሃይማኖቱ ላዕላይ መዋቅር ላይ የተቀመጡ “እረኞች” ምዕመኑ እስከ ቤተ እምነቱ እየተቃጠለ ያለው ለእርሱ የሚቆረቆር፣ የሚደርስልኝ አባት አለኝ በማለት መሆኑን ተገንዝባችሁ ከዓለማዊ መግለጫ ወጥታችሁ የአባትነት ሚናችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን፤
- ከመግለጫ ጋጋታ ባለፈ ቤተ እምነቱንም ሆነ ምዕመናኑን ለመከላከል ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግና ይህን ኢሰብአዊ ድርጊት ለመግታት የሚደረግን እንቅስቃሴ ማህበራችን ይደግፋል፤
- የኦቶማን ቱርክ የክርስትና ሃይማኖትን በጀኖሳይድ በማጥፋት እስላማዊ ሪፐብሊክ እንዳቋቋመው ሁሉ አሁንም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ላይ ላለፉት ስምንት ዓመታት እየሆ ያለው በኦሮምያ ያለውን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኝ በማጥፋት አንድ ወጥ ሃይማኖት ለማስፈን የሚደረግን ዘግናኝ ጭፍጨፋ እንቃወማለን፤
- በጉዳቱ ምክንያት ችግር ውስጥ የገቡ ወገኖቻችንን ሰብአዊ እርዳታ እናደርጋለን፤
- መሰል የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴዎች እንዳይደገሙ ሁሉም ኢትዮጵያዊና ዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
በመጨረሻም ለሰማዕታቱ ወዳጅ ዘመዶችና ለእምነቱ ተከታዮች መጽናናትን እንመኛለን።
የአማራ ማህበር በኦሪገን
