እንኳን ለዐቢይ ጾምና ለሮመዳን ጾም አደረሳችሁ

በዚህ ሳምንት የሁለት አበይት አብያተ ዕምነቶች ሁለት ታላላቅ ጾሞች ተከታትለው ይጀመራሉ። ሰኞ የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማንያን የሚጀምሩት ሊቀ ካህን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾሞ አማንያን ይጾሙት ዘንድ የተሰጠው ዐቢይ ጾም ወይም የሆዳዴ ጾም ይጀምራል። ከሁለት ቀን በኋላ ረቡዕ የካቲት 11 ቀን 2018 ዓ.ም ደግሞ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚጾሙት የታላቁ የሮመዳን ጾም ይጀመራል። በኦሪገን የአማራ ማህበር እንኳን ለጾሙ በሰላም አደረሳችሁ ይላል።

ነቢዩ ኢሳይያስ (58፤6-7) በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ስለጾም እንዲህ ይላል። “እኔስ የመረጥኩት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፣ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፤ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፣ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ ትቆርስ ዘንድ፣ ስደተኞችንና ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፣ የተራቆቱትንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፣ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሸግ አይደለምን?”

ወንጌለኛው ቅዱስ ማቲዎስም (25፤35) ጾማችን ከጠብና ከሙግት በመራቅ ብቻ ሳይሆን መልካም ነገር በመስራት መሆን እንዳለበት የዓለም ቤዛ ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ያሰተማረውን እንዲህ ያዘክራል። “ተርቤ፣ አብልታችሁኛልና፣ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል፣ እንግዳ ሁኜ ተቀብላችሁኛልና፣ ታርዤ አልብሳችሁልኛልና፣ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፣ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና።”

በእስልምና እምነት አስተምህሮ ሮመዳን ትልቁ ጾም ሲሆን አላህን በመፍራት ተቅዋን (የፈጣሪ ፍራቻን) በማዳበር ከጥዋት እስከ ማታ ከምግብ በመከልከል የሚጾም ነው። በዚህ የጾም ጊዜ ያልተቋረጠ ጸሎት ይደረጋል፣ ቁርአን ጥናት ይከናወናል፣ በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖቹን ሰደቃ (ምጽዋት) በማብላትና እርዳታ በማድረግ የሚጾመም ነው።

እነዚህ ታላላቅ እምነቶች እንደሚነግሩን ከሆነ ስንጾም ከምግብ በመለየት ብቻ ሳይሆን በመከራ ውስጥ ያሉና የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብና በመደገፍ መሆን እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው ያሳስባሉ፤ መተግበርም ሃይማኖታዊ ግዴታዎች እንደሆኑ ይናገራሉ። እንግዲያውስ በዚህ ሀገር የምንኖር የአማራ ተወላጆች በሀገር ቤት በመከራ ውስጥ ያለውን፣ መጠለያው የወደመበትን፣ ያለወላጅ/ያለጧሪ የቀሩ ወገኖችን፣ በርሃብ ውስጥ ያሉ ወገኖችን፣ በጾም የዋለ ጎሮሯቸውን የሚያረሰርሱበት ማለፊያ እንጀራ እንኳን የሌላቸውን፣ የአገዛዙን ጅምላ ጭፍጨፋ በመፍራት በስደት ያሉት ህዝባችንን በማሰብ መሆን ይኖርበታል። ከማሰብም በላይ በተግባር የተደገፈ ነገር ማድረግ ያስፈልጋል። በጾም ምክንያት የምናወጣትን የቡና ሂሳብ ብናጠራቅማትና በጾሙ መጨረሻ ተሰባስቦ ቢላክ ለብዙዎቹ ተስፋ ይሆናልና በዚህም ማሰብ ተገቢ ይሆናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ህዝባችን ከተጫነበት ቀንበር፣ ከወረደበት መከራ ፈጣሪ ይታደገው ዘንድ ፈጣሪን መጠየቅ ያስፈልጋል።

በኦሪገን የአማራ ማህበር ስንጾም ለወገኖቻችን አንዳች ነገር በማድረግ መሆን እንዳለበት ያሳስባል። መልካም የዐቢይ ጾም። ሮመዳን ከሪም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *