እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

የአማራ ማህበር በኦሪገን ለመላው አባላቱና ለእምነቱ ተከታዮች እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቱን ይገልጻል። በዓሉን ስናከብር በብዙ መጽናት፥ በመከራ፥ በችግር፥ በጭንቀት፥ በመገረፍ፥ በወኅኒ፥ በሁከት፥ በድካም፥ እንቅልፍ በማጣት፥በርሃብና በመታረዝ ውስጥ ያሉ ወገኖቻችን እያሰብን መሆን ይኖርበታል። በሀገራችን በተለይም ደግሞ በአማራው ህዝብ ላይ እየደረሰ ባለው ኢሰብአዊ ድርጊት የተነሳ በስደት፣ በመጠለያ እንዲሁም በየቤታቸው ሁነውም በተከሰተው የኑሮ ውድነት ምክንያት ቤታቸው የሚበላም፣ የሚጠጣና የሚለበስ ያጡትን ወገኖቻችን በማሰብ መሆን ይኖርበታል። እንዲያ ሲሆን ለሰው ልጅ ደኅነት የተወለደው ክርስቶስ መታሰቢያ በዓል የተሟላ ያደርገዋል። በክርስቶስ መወለድ ‘’በጨለማ የሚኖር ህዝብ ብርሃን አየ” እንደተባለው ሁሉ በመፈናቀል፣ በጦርነትና በኑሮ ውድነት ምክንያት በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖቻችንን በማሰብና የምንችለውን በማድረግ እንዲሆን ማህበሩ ማስታወስ ይፈልጋል።

የገና በዓል የአንድነትና የፍቅር በዓልም ነው። ቤተሰብ እስከ ጎረቤት አብረው በደስታ የሚያከብሩት እንደ መሆኑ መጠን በአንድነትና በፍቅር በመሆን በችግር ውስጥ ያለው ህዝባችን ሰላም አግኝቶ፣ ራሱን ችሎ ከችግር ወጥቶ የሚኖርበት ዘመን እንዲመጣ በጋራ መቆም ይጠበቅብናል። በሀገረ አሜሪካ የሚኖሩ ልጆቻችን የአማራን ባህልና ቱፊት ማሳወቅና ማስተማርም ይጠበቅብናል። በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ እያልን ማለት ነው። በዚሁ አጋጣሚ አንድነትን ማጠናከር አስፈላጊ በመሆኑ ሁሉም ማኅበሩን ለማጠናከር የበኩላችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።  

በድጋሚ ማኀበራችን መልካም የገና በዓል ይመኛል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *