ከታህሳስ 29፣ 2025 እስከ ጥር 4፣ 2026 ባለው የሳምንት ጊዜ ውስጥ በአማራ ፋኖ ራስን የመከላከል ኃይል (ፋኖ) እና በኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ አገዛዝ መካከል በተደረጉ ውጊያዎች ከ34 በላይ በሆኑ የአማራ ክልል ወረዳዎች/ከተማ አስተዳደሮች ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የአማራ ማህበር በአሜሪካ (AAA) በአወጣው ሳምንታዊ ጥናት አስታውቋል። ኢሰብአዊ ድርጊቱ የተፈጸመው በክልሉ ከሚገኙት የአስተዳደር መዋቅሮች ከኦሮሞ ልዩ ዞን ውጪ በሁሉም አካባቢዎች ነው። በተለይም ደግሞ በራያ ባላ፣ በቡግና፣ በስናን፣ በአዋበል፣ በአየሁ ጓጉሳ እና በምዕራብ ደምቢያ ወረዳዎች ሰላማዊ ሰዎች መጎዳታቸውን ጥናቱ አመላክቷል። በኦሮሚያ ክልል በጅማ ዞን ጌራ ወረዳ በአማራ ማህበረሰብ ላይ ጉዳት መድረሱም ተገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ ወከባ፣ እስራትና የመፈናቀል ሥራዎች መቀጠላቸውን ጥናቱ ያሳያል።
በአማራ ክልል በሚገኙ 3 ወረዳ/ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ የድሮን እንቅስቃሴ ተመዝግቧል። እነዚህም በምስራቅ ጎጃም ፣በምዕራብ ጎጃም እና በሰሜን ጎጃም ዞኖች ውስጥ የሚገኙትን የስናን፣ ጃቢ-ጠህናን እና የጎንጂ ቆለላ ወረዳዎችን ያጠቃልላል። በሁለቱ ክስተቶች የዜጎች ጉዳት ደርሷል።
በአማራ ክልል በኮረም፣ በራያ ቆቦ፣ በአምባሰል፣ በሀብሩ እና በወምበርማ ወረዳዎች የሰላማዊ ሰዎች እስራቶች በብልጽግና ወታደሮች መፈጸሙ ተገልጿል። በዋግ ኽምራ ዞን ኮረም ከተማ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሃይሎች በአማራ ተወላጆች ላይ እስራት መፈጸማቸውን ጥናቱ አመልክቷል።
በአዊ ዞን አዮ ጓጉሳ ወረዳ ደግሞ የጠለፋ ክስተት ተመዝግቧል።
በዚህ ሳምንት የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት እና የጸጥታ ኃይሎች በኦሮሚያ ክልል የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የትውልድ ቦታ በሆነችው በጅማ ዞን በሚገኙ የአማራ ጎሳ ነዋሪዎች ላይ በማነጣጠር ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት እና ከባድ ጭቆናን አጠናክረዋል። በዚህ አካባቢ የጸጥታ ሀይሎች በርካታ የአማራ ተወላጆችን ገድለዋል፣ እስራት ፈጽመዋል፣ አፈናዎችንም አካሂደዋል። ከዚህም በተጨማሪ ማህበራዊ ስብሰባዎችን፣ ሃይማኖታዊ አምልኮን፣ የንግድ እንቅስቃሴዎችን፣ በክልል መካከል የሚደረግ ጉዞን እንዳያደርጉ ከመከልከላቸውም በላይ የግል ንብረታቸውን መውረስንና ከባድ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ገደቦችን ተጥሎባቸዋል።
ከአዲስ አበባ ከተማ የተገኙ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት የአማራ ወጣት ልጃገረዶችንና ሴቶችን የሚነኩ የዝሙት አዳሪነትና ሌሎች የብዝበዛ ዓይነቶች አስደንጋጭ ጭማሪ ማሳየታቸውን የአማራ ማህበር በአሜሪካ ያካሄደው ጥናት ያሳያል።

